
ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር በአሜሪካ የሰብዓዊ መብት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ዋነኛው ተፅእኖ ፈጣሪ ነበር። የማርቲን ሉተር ኪንግ ብጥብጥ አልባ ተቃውሞ በአሜሪካ ውስጥ ስላለው የዘር መድልዎ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያስቻለ ነበረ። በዚህም መሠረት ዋነኛ የፖለቲካ ለውጥ አራማጅ ነበረ። ማርቲን ሉተር ኪንግ ከዚህ በተጨማሪ የተዋጣለት ተናጋሪ ነበረ። በዚህ ችሎታውም የበርካታ ሰዎችን አስተሳሰብ እና ልቦና መግዛት ችሏል።
ማርቲን ሉተር ኪንግ ጂኒየር እ.ኤ.አ ጥር 15 ቀን 1929 አትላንታ ውስጥ ተወለደ። አባቱና አያቱ የአፍሪካ አሜሪካውያን ባፕቲስት ቤተክርስቲያን መጋቢዎች ነበሩ። ማርቲን ሉተር ኪንግ አትላንታበሚገኘው ሞርሃውስ ኮሌጅ (የጥቁሮች ኮሌጅ) ከተማረ በኋላ ፔንሲልቫንያ እና ቦስተን ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ስነ መለኮት ሴማናሪ ትምህርቱን ተከታትሏል። በዩኒቨርስቲ ቆይታው ማርቲን ሉተር ኪንግ ጥቁር አሜሪካዊያን ላይ ስለሚደርሰው የእኩልነት መነፈግ እና ኢፍትሐዊ መድሎ ተገነዘበ።
በተለይም በጋንዲ ብጥብጥ አልባ ተቃውሞ ፍልስፍና ተመሰጠ። የጋንዲ ፍልስፍና ከባፕቲስት እምነት አስተምህሮ ጋር የተዛመደ መሆኑን ተገነዘበ። በ24 ዓመቱ ኪንግ ኮሬታ ስኮት የተባለች ቆንጆ እናተሰጥቶ ያላት ወጣት ሴት አገባ። ካገባ በኋላ ኪንግ አላባማ ሞንትጐመሪ ዴክስተር ጐዳና በሚገኘው ባፕቲስት ቤተክርስቲያን ሠባኪ ሆነ።
የሞንትጐመሪ የአውቶቡስ ተቃውሞ
በማርቲን ሉተር ኪንግ ሕይወት ውስጥ የሞንትጐመሪው የአውቶቡስ ተቃውሞ ትርጉም ያለው ለውጥ የፈጠረ ክስተት ነው። ይህንን እንቅስቃሴ ኪንግ በማደራጀት መርቶታል። ይህ ተቃውሞ በሰብዓዊ መብት ትግል ውስጥ ለውጥ ያመጣ እና በርካታ ብሄራዊ ህትመቶችን የሳበ እንቅስቃሴ ነበር።
ጉዳዩ የተከሰተው በቀላል ነገር እ.ኤ.አ ታሕሳስ 5 ቀን 1955 ሮዛ ፓርክስ የተባለች የጥቁር መብት ተሟጋች “ነጮች ብቻ” በሚቀመጡበት የአውቶቡስ ክፍል ተቀምጣ እየተጓዘ ቦታውን ለነጭ እንድትለቅ ስትጠየቅ አሻረፈኝ በማለቷ ነበር። ይህ ጉዳይ በሞንትጐመሪ ውስጥ የጥቁሮች የመብት ክልከላ ላይ የነበረው ጥብቅ የልዩነት ገደብ ላይ ተቃውሞ አስነሳ።
የአውቶቡስ ኩባንያው ጥቁሮችን በመደገፍ በአውቶቡስ ውስጥ የነበረውን ልዩነት እንዲቃወም ጥሪ ቢደረግለት ለመተባበር ፈቃደኛ አልነበረም። በዚህም መሠረት እነ ማርቲን ሉተር ኪንግ በከተማው ውስጥ የሚገኙ ጥቁሮች ምንም ዓይነት የከተማ አውቶቡስ እንዳይጠቀሙ አመፅ ጠሩ። ተቃውሞው ለወራት ዘለቀ፣ ጉዳዩ ወደ ጠቅላላ ፍርድ ቤት ተመራ፣ ፍርድ ቤቱም መድሎው የህገመንግስት ድጋፍ የለውም ሲል ወሠነ።
የሠብዓዊ መብት እንቅስቃሴ
ከሞንትጐመሪው የአውቶቡስ ተቃውሞ እንቅስቃሴ በኋላ የደቡብ ክርስቲያን መሪዎች ኮንፍረንስን አቋቋም። ይህም እየተጠናከረ ለመጣው የጥቁሮች መብት መከበር እንቅስቃሴ ዋና አቀንቃኝ ማሕበር ሆነ። በተለይ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ የጥቁሮች ኃይል እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ወቅት ነበር። በወቅቱ ማልኮልም ኤክስ እና ሌሎች የጥቁር ማንነት አቀነቃኝ ቡድኖች ተጠናከሩ።
ሆኖም ግን ኪንግ ሁል ጊዜ ለብጥብጥ-አልባ ተቃውሞ መርህ ቁርጠኛ ነበር።
የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ንግግሮች
ማርቲን ሉተር ኪንግ አነቃቂ እና ተፅአኖ ፈጣሪ ተናጋሪ ነበር። አድማጮቹን የመመሰጥ እና የማነቃቃት ችሎታ ነበረው። በተለይ የተስፋ ዕይታ ለአድማጮቹ መስጠት ይችልበታል። የወቅቱን ፍትህ መጓደል አውቆታል ነገር ግን ይህ ኢፍትሐዊ ሁኔታ እንደሚያልፍ ደመና እንደሚያልፍ ተሰምቶታል። ኪንግ በተደጋጋሚ ጊዜ ፈጣሪን፣ ቅድስ መጽሐፍንና የክርስትና እምነቱን በመጥቀስ ንግግር ያደርግ ነበር።
ንግግሮቹ በአብዛኛው ከበቀል ነፃ የሆነ፣ በተለይ ወደፊት መራመድ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። በ1963 ታይም መጽሔት የአመቱ ምርጥ ሠው ብሎታል። ይህ የሆነው መለያው የሆነውን “ሕልም አለኝ” የተሰኘ ንግግሩን በዋሽንግተን ዲሲ የሠብዓዊ መብት ሠልፍ ላይ ያቀረበውን ንግግሩን ተከትሎ ነው። በሚቀጥለው ዓመት በማህበራዊ ፍትሕ ላይ ላበረከተው አስተዋፅኦ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሽናፊ ኪንግ ከሽልማቱ ያገኘውን54,23 ዶላር ለሠብዓዊ መብት እንቅስቃሴ እንደሚለግስ አስታወቀ።
የኖቤል ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ ኪንግ የፖለቲካ ሠዎች እንዲያማክራቸው ይጠይቁት ነበር። ለምሳሌ የአሜሪካ ፕሬዝደነት የነበረው ሊንደን ጆንሰንን ያማክር ነበር።
ሆኖም ግን ኪንግ የቪየትናም ጦርነትን በመቃወሙ በጆንሰን አስተዳደር አልተወደደለትም። በወቅቱ ኪንግ በተደጋጋሚ ጊዜ በባለስልጣናት ለምሳሌ በአፍቢአይ ምርመራ ይደረግለት ነበር። “በተራራ ጫፍ ላይ ነበርኩ” የተሰኘ ታዋቂ ንግግሩን ካደረገ በኋላ በሁለተኛው ቀን ተገደለ። ለክብሩ አሜሪካ የማርቲን ሉተር ኪንግ ቀን ሠይማለች። ኪንግ የአሜሪካ ፍትህ እና የዘር እኩልነት አርማ ሆኖ ይቀጥላል።

